የዮሐንስ ወንጌል

እውነተኛ ታሪክ

1
12 ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑት ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን መብት ሰጣቸው።
book-open-2 READ

ቃል ሥጋ ሆነ

1በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። 2እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ። 3ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም። 4ሕይወት በእርሱ ነበረች፤ ይህች ሕይወት የሰው ብርሃን ነበረች። 5ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማውም አላሸነፈውም። 6ከእግዚአብሔር የተላከ ዮሐንስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። 7ሰዎች ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ፣ ስለ ብርሃን ምስክር ሆኖ ለመቆም መጣ፤ 8ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም። 9ለሰው ሁሉ ብርሃን ሰጪ የሆነው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። 10እርሱ በዓለም ውስጥ ነበረ፤ ዓለም የተፈጠረው በእርሱ ቢሆንም እንኳ፣ ዓለም አላወቀውም። 11ወደ ራሱ ወገኖች መጣ፤ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፤ 12ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑት ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን መብት ሰጣቸው። 13እነዚህም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ፣ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። 14ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም አደረ፤ እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን። 15ዮሐንስም፣ “ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ ይልቃል’ ብዬ የመሰከርሁለት እርሱ ነው” በማለት ጮኾ ስለ እርሱ መሰከረ። 16ከእርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል፤ 17ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። 18ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ እቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው።

2
19 “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ እኔም በሦስት ቀን መልሼ አነሣዋለሁ” ብሎ መለሰላቸው።
book-open-2 READ

ኢየሱስ ቤተ መቅደስን አጠራ

12ከዚህ በኋላ ከእናቱ፣ ከወንድሞቹና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በዚያም ጥቂት ቀን ተቀመጡ። 13የአይሁድ ፋሲካም እንደ ተቃረበ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 14በቤተ መቅደሱ አደባባይ ከብቶችን፣ በጎችንና ርግቦችን የሚሸጡ እንዲሁም ተቀምጠው የገንዘብ ምን ዛሪ የሚያከናውኑ ሰዎች አገኘ። 15የገመድ ጅራፍ አበጅቶ በጎችንና ከብቶችን ሁሉ ከቤተ መቅደሱ ግቢ አባረረ፤ የመንዛሪዎችን ገንዘብ በተነ፤ ጠረጴዞቻቸውንም ገለበጠ። 16ርግብ ሻጮችንም፣ “እነዚህን ከዚህ አስወጧቸው፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት!” አላቸው። 17ደቀ መዛሙርቱም፣ “ለቤትህ ያለኝ ቅናት ያቃጥለኛል” ተብሎ የተጻፈው ትዝ አላቸው። 18አይሁድም፣ “ይህን ሁሉ ለማድረግ ሥልጣን እንዳለህ የሚያረጋግጥ ምን ታምራዊ ምልክት ታሳየናለህ?” አሉት። 19ኢየሱስም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ እኔም በሦስት ቀን መልሼ አነሣዋለሁ” ብሎ መለሰላቸው። 20አይሁድም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ ለመሥራት አርባ ስድስት ዓመት ፈጅቶአል፤ ታዲያ አንተ እንዴት በሦስት ቀን መልሰህ ታነሣዋለህ?” አሉት። 21ቤተ መቅደስ ሲል ግን፣ ስለ ገዛ ሰውነቱ መናገሩ ነበር። 22ከሙታንም ከተነሣ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱ ምን እንደ ተናገረ አስታወሱ፤ መጻሕፍትንና ኢየሱስ ያለውንም ቃል አመኑ። 23በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ፣ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ታምራት አይተው በስሙ አመኑ፤ 24ኢየሱስ ግን ሰውን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ አይታመንባቸውም ነበር፤ 25በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ ስለ ነበር፣ ማንም ስለ ሰው እንዲመሰክርለት አላስፈለገውም።

3
16 “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤
book-open-2 READ

ኢየሱስ ኒቆዲሞስን አስተማረ

1ከፈሪሳውያን ወገን፣ ከአይሁድ አለቆች አንዱ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ ሰው ነበረ፤ 2በሌሊትም ወደ ኢየሱስ መጥቶ፣ “ረቢ፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ ሰው በቀር አንተ የምታደርጋቸውን ታምራዊ ምልክቶች ማንም ሊያደርግ ስለማይችል፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣህ መምህር እንደሆንህ እናውቃለን” አለው። 3ኢየሱስም መልሶ፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” አለው። 4ኒቆዲሞስም፣ “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ እንዲወለድ ተመልሶ ወደ እናቱ ማሕፀንስ ሊገባ ይችላልን?” አለው። 5ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤ 6ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደም መንፈስ ነው። 7‘ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ’ ስላልሁህ አትገረም፤ 8ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደ መጣ፣ ወዴት እንደሚሄድም አታውቅም፤ ከመንፈስም የተወለደ ሁሉ እንደዚሁ ነው።” 9ኒቆዲሞስም፣ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ጠየቀው። 10ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ሳለ እነዚህን ነገሮች አታውቅምን? 11እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉም። 12ስለ ምድራዊው ነገር ነግሬአችሁ ያላመናችሁ፣ ስለ ሰማያዊው ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? 13ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር፣ ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም። 14ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ፣ የሰው ልጅም እንዲሁ ሊሰቀል ይገባዋል፤ 15ይኸውም በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው። 16“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤ 17እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ለመፍረድ ሳይሆን፣ ዓለምን በእርሱ ለማዳን ነው። 18በእርሱ የሚያምን ሁሉ አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ፣ አሁኑኑ ተፈርዶበታል። 19ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ነበረ፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ፤ 20ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ አድራጎቱም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። 21በእውነት የሚመላለስ ግን ሥራው በእግዚአብሔር የተሠራ መሆኑ በግልጽ ይታይ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።”

4
14 እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ከቶ አይጠማም፤
book-open-2 READ

ኢየሱስ ከአንዲት ሳምራዊት ጋር ተነጋገረ

1ፈሪሳውያን ከዮሐንስ ይልቅ ኢየሱስ ብዙ ደቀ መዛሙርትን እንዳፈራና እንዳጠመቀ ሰሙ፤ 2ዳሩ ግን ያጠመቀው ኢየሱስ ሳይሆን ደቀ መዛሙርቱ ነበሩ። 3ጌታም ይህን እንዳወቀ ይሁዳን ለቆ ወደ ገሊላ ተመልሶ ሄደ። 4በሰማርያም በኩል ማለፍ ነበረበት። 5ስለዚህ በሰማርያ፣ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ቦታ አጠገብ ወደ ነበረች፣ ሲካር ወደምትባል ከተማ መጣ። 6በዚያም የያዕቆብ የውሃ ጒድጓድ ነበረ፤ ኢየሱስም ከጒዞው የተነሣ ደክሞት ስለ ነበር በውሃው ጒድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ነበር። 7አንዲት ሳምራዊት ሴት ውሃ ለመቅዳት ስትመጣ ኢየሱስ፣ “እባክሽ የምጠጣው ስጪኝ” አላት፤ 8ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ለመግዛት ወደ ከተማ ሄደው ነበር። 9ሳምራዊቷም፣ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ፣ እኔን ሳምራዊቷን እንዴት ውሃ አጠጪኝ ትላለህ?” አለችው፤ ይህን ማለቷ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር ስለማይተባበሩ ነው። 10ኢየሱስም፣ “የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂና ውሃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ፣ አንቺው በጠየቅሽው፣ እርሱም የሕይወትን ውሃ በሰጠሽ ነበር” ሲል መለሰላት። 11ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ፣ መቅጃ የለህም፤ ጒድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ታዲያ ይህን የሕይወት ውሃ ከየት ታገኛለህ? 12ለመሆኑ አንተ፣ ይህን ጒድጓድ ከሰጠን፣ ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እርሱ ራሱና ልጆቹ፣ እንስሳቱም ከዚሁ ጒድጓድ ጠጥተዋል።” 13ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላት፤ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ እንደ ገና ይጠማል፤ 14እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት ውሃ ምንጭ ይሆናል።” 15ሴትዮዋም፣ “ጌታዬ፤ እንዳልጠማና ውሃ ለመቅዳት እንዳልመላለስ፣ እባክህ ይህን ውሃ ስጠኝ” አለችው። 16እርሱም፣ “ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ተመለሽ” አላት። 17ሴትዮዋም፣ “ባል የለኝም” ብላ መለሰች። ኢየሱስም፣ እንዲህ አላት፤ “ባል የለኝም ማለትሽ ትክክል ነው፤ 18በርግጥ አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁን ከአንቺ ጋር ያለውም ባልሽ ስላልሆነ፣ የተናገርሽው እውነት ነው።” 19ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ፣ አንተ ነቢይ እንደሆንህ አያለሁ፤ 20አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ ሰገዱ፤ እናንተ አይሁድ ግን ሰው መስገድ ያለበት በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ” አለችው። 21ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “አንቺ ሴት፤ በዚህ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ እንደሚመጣ እመኚኝ። 22እናንተ ሳምራውያን ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ ግን ድነት ከአይሁድ ስለ ሆነ ለምናውቀው እንሰግዳለን። 23በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቶአል፤ አብም እንደዚህ በእውነት የሚሰግዱለትን ይፈልጋል። 24እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል።” 25ሴትዮዋም፣ “ክርስቶስ የተባለ መሲሕ እንደሚመጣ ዐውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ነገር ይነግረናል” አለችው። 26ኢየሱስም፣ “የማነጋግርሽ እኮ እኔ እርሱ ነኝ” ሲል ገልጦ ነገራት። 27በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው መጡ፤ ከሴት ጋር ሲነጋገር በማግኘታቸው ተደነቁ፤ ሆኖም ግን፤ “ምን ፈለግህ?” ወይም፣ “ከእርሷ ጋር የምትነጋገረው ለምንድን ነው?” ብሎ የጠየቀው ማንም አልነበረም። 28ሴትዮዋም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ተመለሰች፤ ለሕዝቡም፣ 29“ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እርሱ ክርስቶስ ይሆን እንዴ?” አለች፤ 30እነርሱም ከከተማ ወጥተው እርሱ ወዳለበት አመሩ። 31በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ፣ “ረቢ፣ እህል ቅመስ እንጂ” አሉት። 32እርሱ ግን፣ “እናንተ የማታውቁት፣ የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው። 33ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሰው ምግብ አምጥቶለት ይሆን እንዴ?” ተባባሉ። 34ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው፤ 35እናንተ፣ ‘ከአራት ወር በኋላ መከር ይደርሳል’ ትሉ የለምን? እነሆ፣ አዝመራው ለመከር እንደ ደረሰ ቀና ብላችሁ ማሳውን ተመልከቱ እላችኋለሁ። 36አጫጁ አሁንም ቢሆን እንኳ ደመወዙን እየተቀበለ ነው፤ ለዘላለም ሕይወት ይሆን ዘንድ አዝመራውን ይሰበስባል፤ ይህም ዘሪውና አጫጁ በጋራ ደስ እንዲላቸው ነው። 37ስለዚህ፣ ‘አንዱ ይዘራል፤ ሌላውም ያጭዳል’ የተባለው ምሳሌ እውነት ነው። 38ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ አድካሚውን ሥራ ሌሎች ሠሩ፤ እናንተም የድካማቸውን ፍሬ ሰበሰባችሁ።” 39ሴትዮዋ፣ “ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ” ብላ ስለ መሰከረች፣ ከዚያች ከተማ ብዙ ሳምራውያን በእርሱ አመኑ። 40ስለዚህ፣ ሳምራውያኑ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ አብሮአቸው እንዲቈይ አጥብቀው ለመኑት፤ እዚያም ሁለት ቀን ቈየ። 41ከቃሉም የተነሣ ሌሎች ብዙዎች አመኑ። 42ሴትዮዋንም፣ “ከእንግዲህ የምናምነው አንቺ ስለ ነገርሽን ብቻ አይደለም፤ እኛ ራሳችን ሰምተነዋል፤ ይህ ሰው በእውነት የዓለም አዳኝ እንደሆነ እናውቃለን” አሏት።

5
24 “እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ፣ በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤
book-open-2 READ

ወልድ ሕይወትን ይሰጣል

16አይሁድም፣ በሰንበት ቀን እነዚህን ድርጊቶች በመፈጸሙ፣ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር። 17ኢየሱስም፣ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ” አላቸው። 18እንግዲህ አይሁድ፣ ኢየሱስ ሰንበትን ስለሻረ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አባቱ በማድረግ፣ ራሱን ከእግዚአብሔር እኩል በማድረጉ፣ ሊገድሉት አጥብቀው ይፈልጉት ነበር። 19ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ አብ ሲሠራ ያየውን ብቻ እንጂ ወልድ ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ያደርጋልና፤ 20አብ ወልድን ስለሚወድ የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል፤ ትደነ ቁም ዘንድ ከእነዚህም የሚበልጥ ነገር ያሳየዋል። 21ምክንያቱም አብ ሙታንን እንደሚያስነሣ፣ ሕይወትንም እንደሚሰጥ፣ ወልድም ደግሞ ለሚፈቅደው ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል። 22አብ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ነገር ግን ፍርድን ሁሉ ለወልድ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ 23ይኸውም፣ ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ ወልድን የማያከብር፣ የላከውን አብንም አያከብርም። 24 “እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ፣ በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። 25እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቶአል፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። 26አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው ሁሉ፣ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና፤ 27ወልድ የሰው ልጅ ስለ ሆነም እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል። 28 “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ 29መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ። 30እኔ ብቻዬን ከራሴ ምንም ማድረግ አልችልም፤ የምፈርደው የምሰማውን ብቻ ነው፤ የላከኝን እንጂ የራሴን ፈቃድ ስለማልሻም ፍርዴ ትክክል ነው።

6
35 “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔም የሚያምን ፈጽሞ አይጠማም።
book-open-2 READ

ኢየሱስ የሕይወት እንጀራ

25ከባሕሩ ማዶ ባገኙትም ጊዜ፣ “ረቢ፤ መቼ ወደዚህ መጣህ?” አሉት። 26ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ እንጂ፣ ታምራዊ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም። 27ለሚጠፋ እንጀራ አትሥሩ፤ ነገር ግን የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር ምግብ ሥሩ፤ ለዚህም እግዚአብሔር አብ ማረጋገጫ ማኅተሙን በእርሱ ላይ አትሞአልና።” 28እነርሱም፣ “ታዲያ የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን ማድረግ አለብን?” አሉት። 29ኢየሱስም፣ “እርሱ በላከው ታምኑ ዘንድ፣ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው” ሲል መለሰላቸው። 30ስለዚህ እንዲህ ብለው ጠየቁት፤ “አይተን እንድናምንህ ምን ታምራዊ ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? 31‘ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራን ሰጣቸው’ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ።” 32ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ እውነተኛውን እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ ግን አባቴ ነው፤ 33የእግዚአብሔር እንጀራ እርሱ ከሰማይ የሚወርድ፣ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና።” 34እነርሱም፣ “ጌታ፣ እንግዲያውስ ይህን እንጀራ ሁል ጊዜ ስጠን” አሉት። 35ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔም የሚያምን ፈጽሞ አይጠማም። 36ነገር ግን እንደ ነገርኋችሁ፣ አይታችሁኝም እንኳ አታምኑም። 37አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤ 38ከሰማይ የወረድሁት የራሴን ፈቃድ ለማድረግ ሳይሆን፣ የላከኝን የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም ነውና፤ 39የላከኝም ፈቃድ፣ ከሰጠኝ ሁሉ አንድ እንኳ ሳይጠፋብኝ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣ ነው። 40የአባቴ ፈቃድ ወልድን አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።” 41አይሁድም፣ “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ” በማለቱ ያጒረመርሙበት ጀመር። 42ደግሞም፣ “ይህ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው፣ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? ታዲያ አሁን እንዴት፣ ‘ከሰማይ ወረድሁ ይላል’” አሉ። 43ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሳችሁ አታጒረምርሙ፤ 44የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ማንም ወደ እኔ መምጣት አይችልም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። 45በነቢያትም፣ ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ ተጽፎአል፤ አብን የሚሰማና ከእርሱም የሚማር ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። 46ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሆነው በቀር አብን ያየ ማንም የለም፤ አብን ያየው እርሱ ብቻ ነው። 47እውነት እላችኋለሁ፤ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው። 48የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። 49አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ይሁን እንጂ ሞቱ። 50ነገር ግን ሰው እንዳይሞት ይበላው ዘንድ ከሰማይ የሚወርድ እንጀራ ይህ ነው። 51ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ ይህም እንጀራ፣ ለዓለም ሕይወት እንዲሆን የምሰጠው ሥጋዬ ነው።” 52አይሁድም፣ “እንበላ ዘንድ ይህ ሰው ሥጋውን እንዴት ሊሰጠን ይችላል?” እያሉ እርስ በርሳቸው አጥብቀው ይከራከሩ ጀመር። 53ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋውን ካልበላችሁና ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። 54ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፤ 55ሥጋዬ እውነተኛ ምግብ፣ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፤ 56ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። 57ሕያው አብ እንደ ላከኝ፣ እኔም ከእርሱ የተነሣ በሕይወት እንደምኖር፣ የሚበላኝም እንዲሁ ከእኔ የተነሣ በሕይወት ይኖራል። 58ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በሉ፤ ሞቱም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ግን ለዘላለም ይኖራል።” 59ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም፣ በምኲራብ እያስተማረ ሳለ ነበር።

8
12 “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝም የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ ከቶ በጨለማ አይመላለስም” አላቸው።
book-open-2 READ

የኢየሱስ ምስክርነት እውነት መሆኑ

12ኢየሱስ እንደ ገና ለሰዎቹ፣ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝም የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ ከቶ በጨለማ አይመላለስም” አላቸው። 13ፈሪሳውያንም፣ “አንተ ስለ ራስህ ስለምት መሰክር፣ ምስክርነትህ ተቀባይነት የለውም” አሉት። 14ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ከየት እንደ መጣሁና ወዴት እንደምሄድ ስለማውቅ ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከየት እንደ መጣሁ ወይም ወዴት እንደምሄድ የምታውቁት ነገር የለም። 15እናንተ እንደ ሰው አስተሳሰብ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በማንም አልፈርድም፤ 16ብፈርድም፣ ከላከኝ ከአብ ጋር እንጂ ብቻዬን ስላልሆንሁ ፍርዴ ትክክል ነው። 17የሁለት ሰዎች ምስክርነት ተቀባይነት እንዳለው በሕጋችሁ ተጽፎአል። 18ስለ ራሴ የምመሰክር አንዱ እኔ ነኝ፤ ሌላውም ምስክሬ የላከኝ አብ ነው።” 19ከዚያም፣ “አባትህ የት ነው?” አሉት። ኢየሱስም፣ “አባቴንም እኔንም አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ፣ አባቴንም ባወቃችሁ ነበር” ሲል መለሰላቸው። 20ኢየሱስ ይህን የተናገረው በቤተ መቅደሱ ግቢ፣ በግምጃ ቤት አጠገብ ሲያስተምር ነበር፤ ይሁን እንጂ ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም።

9
3 “እርሱ ወይም ወላጆቹ ኀጢአት አልሠሩም፤ ይህ የሆነው ግን የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ ሕይወት እንዲገለጥ ነው።
book-open-2 READ

ኢየሱስ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ፈወሰ

1በመንገድ ሲያልፍም ከተወለደ ጀምሮ ዐይነ ስውር የሆነ ሰው አየ። 2ደቀ መዛሙርቱም፣ “ረቢ፤ ይህ ሰው ዐይነ ስውር ሆኖ እንዲወለድ ኀጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ራሱ ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጠየቁት። 3ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እርሱ ወይም ወላጆቹ ኀጢአት አልሠሩም፤ ይህ የሆነው ግን የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ ሕይወት እንዲገለጥ ነው። 4ቀን ሳለ፣ የላከኝን ሥራ መሥራት አለብን፤ ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል፤ 5በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ።” 6ይህን ካለ በኋላ፣ በምድር ላይ እንትፍ ብሎ በምራቁ ጭቃ አበጀ፤ የሰውየውንም ዐይን ቀባና፣ 7“ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው፤ ሰሊሆም ማለት ‘የተላከ’ ማለት ነው። ሰውየውም ሄዶ ታጠበ፤ እያየም ተመልሶ መጣ። 8ጎረቤቶቹና ከዚህ ቀደም ብሎ ሲለምን ያዩት ሰዎች፣ “ይህ ሰው ተቀምጦ ሲለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። 9አንዳንዶቹም፣ “በርግጥ እርሱ ነው” አሉ። ሌሎችም፣ “ይመስለዋል እንጂ እርሱ አይደለም” አሉ። እርሱ ግን፣ “እኔው ነኝ” አለ። 10እነርሱም፣ “ታዲያ ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” ሲሉ ጠየቁት። 11እርሱም፣ “ኢየሱስ የሚሉት ሰው ጭቃ አድርጎ ዐይኔን ቀባኝ፤ ወደ ሰሊሆም ሄጄ እንድታጠብም ነገረኝ፤ ሄጄ ታጠብሁ፤ ማየትም ቻልሁ” ሲል መለሰ። 12እነርሱም፣ “ታዲያ፣ ያ ሰው የት አለ?” አሉት። እርሱም፣ “እኔ አላውቅም” አለ።

10
11 “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል፤
book-open-2 READ

እረኛና መንጋው

1 “እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች ጒረኖ በበሩ ሳይሆን፣ በሌላ በኩል ዘሎ የሚገባ ሌባና ነጣቂ ነው፤ 2በበሩ የሚገባ ግን እርሱ የበጎቹ እረኛ ነው፤ 3በር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱንም በጎች በየስማቸው እየጠራ ያወጣቸዋል። 4የራሱ የሆኑትንም ሁሉ ካወጣ በኋላ ፊት ፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። 5እንግዳ የሆነውን ግን ድምፁን ስለማያውቁ ከእርሱ ይሸሻሉ እንጂ ፈጽሞ አይከተሉትም።” 6ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን ምን እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም። 7ስለዚህ ኢየሱስ ዳግም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ የበጎች በር እኔ ነኝ። 8ከእኔ በፊት የመጡት ሁሉ ሌቦችና ቀማኞች ነበሩ፤ በጎቹ ግን አልሰሟቸውም። 9በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ሁሉ ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል። 10ሌባው ሊሰርቅ፣ ሊገድልና ሊያጠፋ ብቻ ይመጣል፤ እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ።” 11 “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል፤ 12ተቀጣሪው እረኛ ግን በጎቹ የእርሱ ስላልሆኑ፣ ተኵላ ሲመጣ ጥሎአቸው ይሸሻል፤ ተኵላውም በጎቹን ይነጥቃል፤ ይበትናቸዋልም። 13የሚሸሸውም ተቀጣሪ ስለ ሆነና ለበጎቹ ደንታ ስለሌለው ነው። 14 “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ እነርሱም ያውቁኛል፤ 15ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው ነው። ሕይወቴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። 16ከዚህ ጒረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት አለብኝ። እነርሱም ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። 17መልሼ ለማንሣት ሕይወቴን አሳልፌ ስለምሰጥ አባቴ ይወደኛል። 18ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ አሳልፌ ለመስጠትም ሆነ ለማንሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልሁትም ከአባቴ ነው።” 19ከዚህም ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ተፈጠረ። 20ብዙዎቹም፣ “ጋኔን ያደረበት እብድ ነው፤ ለምን ትሰሙ ታለችሁ?” አሉ። 21ሌሎች ግን፣ “ይህ ጋኔን ያደረበት ሰው ንግግር አይደለም፤ ጋኔን የዐይነ ስውርን ዐይን መክፈት ይችላልን?” አሉ።

12
24 እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች።
book-open-2 READ

ኢየሱስ ስለ ሞቱ አስቀድሞ ተናገረ

20ለአምልኮ ወደ በዓሉ ከወጡት መካከል የግሪክ ሰዎችም ነበሩ። 21እነርሱም በገሊላ ከምትገኘው ከቤተ ሳይዳ ወደ ሆነው ሰው፣ ወደ ፊልጶስ መጥተው፣ “ጌታው፤ እባክህን፣ ኢየሱስን ለማየት እንፈልጋለን” አሉት። 22ፊልጶስም፤ ለእንድርያስ ሊነግረው ሄደ፤ እንድርያስና ፊልጶስም ለኢየሱስ ነገሩት። 23ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የሰው ልጅ የሚከብርበት ሰዓቱ ደርሶአል፤ 24እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። 25ሕይወቱን የሚወድ ያጣታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል። 26የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔም ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝንም አባቴ ያከብረዋል።

13
34 “አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።
book-open-2 READ

31ይሁዳ ከወጣ በኋላ፣ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “አሁን የሰው ልጅ ከበረ፤ በእርሱም እግዚአብሔር ከበረ። 32እንግዲህ እግዚአብሔር በእርሱ ከከበረ፣ እግዚአብሔር ልጁን በራሱ ዘንድ ያከብረዋል፤ ወዲያውም ያከብረዋል። 33 “ልጆቼ ሆይ፤ ከእናንተ ጋር የምቈየው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድ፣ ‘እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’ እንዳልኋቸው፣ አሁንም ለእናንተ ይህንኑ እላችኋለሁ። 34 “አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። 35እርስ በርሳችሁ ብት ዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”

14
6 “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።
27 ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም።
book-open-2 READ

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን አበረታታ

1 “ልባችሁ አይጨነቅ፤ በእግዚአብሔር እመኑ ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ። 2በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ ይህ ባይሆንማ ኖሮ እነግራችሁ ነበር፤ የምሄደውም ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ነው። 3ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋር እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ። 4እኔ ወደምሄድበትም ስፍራ የሚያደርሰውን መንገድ ታውቃላችሁ።” 5ቶማስም፣ “ጌታ ሆይ፤ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም፤ ታዲያ፣ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” አለው። 6ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። 7እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር። ከአሁን ጀምሮ ግን ታውቁታላችሁ፤ አይታችሁታልም።” 8ፊልጶስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው። 9ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንተ ፊልጶስ! ይህን ያህል ጊዜ ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ፣ ‘አብን አሳየን’ ትላለህ? 10እኔ በአብ እንዳለሁ፣ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? የምነግራችሁ ቃል ከራሴ አይደለም፤ ነገር ግን ሥራውን የሚሠራው በእኔ የሚኖረው አብ ነው። 11እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ ስነግራችሁ እመኑኝ፤ ሌላው ቢቀር ስለ ድንቅ ሥራዎቹ እንኳ እመኑ። 12እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ፣ ከእነዚህም የሚበልጥ ያደርጋል። 13አብ በወልድ እንዲከብር፣ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ፤ 14ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትለምኑኝ፣ እኔ አደርገዋለሁ።

ስለ መንፈስ ቅዱስ የተሰጠ ተስፋ

15 “ብትወዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ። 16እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ 17እርሱም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም። እናንተ ግን፣ አብሮአችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስለሚሆን ታውቁታላችሁ። 18ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። 19ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ዓለም ከቶ አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ። እኔ ሕያው ስለ ሆንሁ እናንተም ሕያዋን ትሆናላችሁ። 20እኔ በአባቴ እንዳለሁ፣ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ፣ እኔም ደግሞ በእናንተ እንዳለሁ በዚያ ቀን ትረዳላችሁ። 21የሚወደኝ ትእዛዜን ተቀብሎ የሚጠብቅ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።” 22ከዚያም የአስቆሮቱ ያልሆነው ይሁዳ፣ “ጌታ ሆይ፣ ታዲያ፣ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ የምትገልጠው እንዴት ነው?” አለው። 23ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ ወደ እርሱ እንመጣለን፤ ከእርሱም ጋር እንኖራለን። 24የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም። ይህ የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። 25 “አሁን ከእናንተ ጋር እያለሁ ይህን ሁሉ ነግሬአችኋለሁ፤ 26አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል። 27ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም። ልባችሁ አይጨነቅ፤ አይፍራም። 28 “ ‘እሄዳለሁ፤ ተመልሼም ወደ እናንተ እመጣለሁ’ ማለቴን ሰምታችኋል፤ ብትወዱኝስ አብ ከእኔ ስለሚበልጥ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ 29የተናገርሁት ሲፈጸም እንድታምኑ፣ ከመሆኑ በፊት አሁን ነግሬአችኋለሁ። 30የዚህ ዓለም ገዥ ስለሚመጣ ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም። እርሱም በእኔ ላይ ሥልጣን የለውም፤ 31ነገር ግን እኔ አብን እንደምወድ፣ አባቴ ያዘ ዘኝንም እንደማደርግ ዓለም እንዲያውቅ ነው። “ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ።”

15
5 “እኔ የወይን ተክል ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ማንም በእኔ ቢኖር እኔም በእርሱ ብኖር፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና።
13 ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ማንም የለውም፤
book-open-2 READ

የወይን ግንድና ቅርንጫፎቹ

1 “እውነተኛው የወይን ተክል እኔ ነኝ፤ አትክልተኛውም አባቴ ነው። 2እርሱም በእኔ ያለውን፣ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ቈርጦ ይጥለዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ግን የበለጠ እንዲያፈራ ይገርዘዋል። 3ከነገርኋችሁ ቃል የተነሣ እናንተ አሁን ንጹሓን ናችሁ። 4በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ እኖራለሁ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ካልሆነ በቀር ብቻውን ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ እናንተም በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ልታፈሩ አትችሉም። 5 “እኔ የወይን ተክል ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ማንም በእኔ ቢኖር እኔም በእርሱ ብኖር፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና። 6በእኔ የማይኖር ተጥሎ እንደሚደርቅ ቅርንጫፍ ነው፤ እንዲህ ያሉት ቅርንጫፎች ተለቅመው ወደ እሳት ይጣላሉ፤ ይቃጠላሉም። 7በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ፣ የምትፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ለምኑ፤ ይሰጣችኋልም። 8ብዙ ፍሬ በማፍራት ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ብትገልጡ፣ በዚህ አባቴ ይከብራል። 9 “አብ እንደ ወደደኝ ሁሉ እኔም ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። 10እኔ የአባቴን ትእዛዝ ጠብቄ በፍቅሩ እንደምኖር፣ እናንተም ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። 11ደስታዬ በእናንተ እንዲሆንና ደስታችሁም ሙሉ እንዲሆን ይህን ነግሬአችኋለሁ። 12ትእዛዜ ይህች ናት፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። 13ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ማንም የለውም፤ 14የማዛችሁን ብትፈጽሙ ወዳጆቼ ናችሁ። 15ከእንግዲህ አገልጋዮች አልላችሁም፤ አገልጋይ ጌታው የሚሠራውን አያውቅምና፤ ነገር ግን ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ስለ ገለጽሁላችሁ ወዳጆች ብያችኋለሁ። 16እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ እንድት ሄዱና ፍሬ እንድታፈሩ ፍሬያችሁም እንዲኖር ሾምኋችሁ። ስለዚህም አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። 17እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ፣ ትእዛዜ ይህቺ ናት።

17
14 ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ፣ እነርሱም ከዓለም ባለመሆናቸው ዓለም ጠልቶአቸዋል።
book-open-2 READ

ኢየሱስ ስለ ራሱ መጸለዩ

1ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “አባት ሆይ፤ ጊዜው ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤ 2ከአንተ ለተቀበላቸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት እንዲሰጥ በሰው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥተኸዋልና። 3እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። 4የሰጠኸኝን ሥራ በመፈጸም በምድር አከበርሁህ። 5እንግዲህ አባት ሆይ፤ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር በአንተ ዘንድ አክብረኝ። 6 “ለእነዚህ ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ። የአንተ ነበሩ ለእኔ ሰጠኸኝ፤ እነርሱም ቃልህን ጠብቀዋል። 7የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደሆነ አሁን ዐውቀዋል፤ 8ምክንያቱም የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸው ተቀብለዋል፤ እኔም ከአንተ እንደ ወጣሁ በርግጥ ዐውቀዋል፤ አንተ እንደላክኸኝም አምነዋል፤ 9እነርሱ የአንተ ስለሆኑ እጸልይላቸዋለሁ፤ ለሰጠኸኝና የአንተ ለሆኑት እንጂ ለዓለም አልጸልይም። 10የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነውም ሁሉ የእኔ ነው፤ በእነርሱም ከብሬአለሁ። 11ከእንግዲህ እኔ በዓለም አልቈይም፤ እነርሱ ግን በዓለም ውስጥ ናቸው፤ እኔም ወደ አንተ መምጣቴ ነው። ቅዱስ አባት ሆይ፤ እኛ አንድ እንደሆንን፣ እነርሱም አንድ እንዲሆኑ በሰጠኸኝ በስምህ ጠብቃቸው። 12እኔ ከእነርሱ ጋር ሳለሁ፣ በሰጠኸኝ ስም ከለልኋቸው፤ ጠበቅኋቸውም፤ የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ከአንዱ ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም። 13 “አሁን ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ ነገር ግን ደስታዬ በእነርሱ ዘንድ የተሟላ እንዲሆን፣ አሁን በዓለም እያለሁ ይህን እናገራለሁ። 14ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ፣ እነርሱም ከዓለም ባለመሆናቸው ዓለም ጠልቶአቸዋል። 15የምለምንህም ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ፣ ከዓለም እንድታወጣቸው አይደለም። 16እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ፣ እነርሱም ከዓለም አይደሉም። 17ቃልህ እውነት ነው፤ በእውነትህ ቀድሳቸው። 18አንተ ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እኔም ወደ ዓለም ልኬአቸዋለሁ። 19እነርሱ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ፣ ራሴን ስለ እነርሱ ቀድሻለሁ። 20 “የእነርሱን ትምህርት ተቀብለው በእኔ ለሚያምኑ ጭምር እንጂ ለእነዚህ ብቻ አልጸልይም፤ 21ይህም፣ አባት ሆይ፤ አንተ በእኔ፣ እኔም በአንተ እንዳለሁ ሁሉም አንድ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም አንተ እኔን እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፣ እነርሱም በእኛ እንዲሆኑ ነው። 22እኛ አንድ እንደሆንን እነርሱም አንድ እንዲሆኑ፣ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ። 23ይህም እኔ በእነርሱ፣ አንተም በእኔ መሆንህ ነው። አንተ እንደ ላክኸኝና እኔን በወደድኸኝ መጠን እነርሱንም እንደ ወደድሃቸው ዓለም ያውቅ ዘንድ፣ አንድነታቸው ፍጹም ይሁን። 24 “አባት ሆይ፤ እነዚህ የሰጠኸኝ፣ እኔ ባለሁበት እንዲሆኑ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝንም ክብሬን እንዲያዩ እፈልጋለሁ። 25 “ጻድቅ አባት ሆይ፤ ዓለም ባያውቅህም፣ እኔ ዐወቅሃለሁ፤ እነዚህም አንተ እንደ ላከኸኝ ያውቃሉ። 26ለእኔ ያለህ ፍቅር በእነርሱ እንዲሆን፣ እኔም በእነርሱ እንድሆን፣ አንተን እንዲያውቁ አድርጌአለሁ፤ እንዲያውቁህም አደርጋለሁ።

19
30 ኢየሱስም ሆምጤውን ከተቀበለ በኋላ፣ “ተፈጸመ” አለ፤ ራሱን አዘንብሎ፣ መንፈሱን አሳልፎ ሰጠ።
book-open-2 READ

የኢየሱስ መሞት

28ከዚያም ኢየሱስ ሁሉ ነገር እንደ ተፈጸመ ዐውቆ፣ የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም፣ “ተጠማሁ” አለ። 29በዚያም የሆመጠጠ ወይን የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሰፍነግ በወይን ጠጅ ነክረው፣ በሂሶጵ ዘንግ ወደ አፉ አቀረቡለት፤ 30ኢየሱስም ሆምጤውን ከተቀበለ በኋላ፣ “ተፈጸመ” አለ፤ ራሱን አዘንብሎ፣ መንፈሱን አሳልፎ ሰጠ። 31ዕለቱ ለሰንበት መዘጋጃ ቀን ነበር። አይሁድ፣ የተሰቀሉት ሰዎች ሬሳ በሰንበት ቀን በመስቀል ላይ እንዳይውል ስለ ፈለጉና ያም የተለየ ሰንበት ስለ ነበር፣ የተሰቀሉት ሰዎች ጭናቸው ተሰብሮ በድናቸው እንዲወርድ ጲላጦስን ለመኑት። 32ስለዚህም ወታደሮቹ መጥተው ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎ የነበረውን የመጀመሪያውን ሰው ጭን ሰበሩ፤ ደግሞም የሌላውን ጭን ሰበሩ። 33ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን ሞቶ ስላገኙት ጭኖቹን አልሰበሩም፤ 34ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ የኢየሱስን ጐን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውሃ ፈሰሰ። 35ይህን ያየው ሰው ምስክርነቱን ሰጥቶአል፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ እውነትን እንደሚናገርም ያውቃል፤ እናንተም እንድታምኑ ይመሰክራል። 36ይህም የሆነው፣ መጽሐፍ፣ “ከአጥንቱ አንድም አይሰበርም” ያለው እንዲፈጸም፣ 37ሌላውም መጽሐፍ፣ “የወጉትም ያዩታል” ስለሚል ነው።

20
19 ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።
book-open-2 READ

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ታየ

19በዚያኑ ዕለት፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን በምሽት፣ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን በመፍራት በሮቹን ቈልፈው ተሰብስበው ሳለ፣ ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። 20ይህንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርትም ጌታን ባዩት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው። 21ኢየሱስም እንደ ገና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እኔን እንደ ላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው። 22ይህን ካለ በኋላም፣ እፍ አለባቸውና እንዲህ አላቸው፤ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ 23የሰዎችን ኀጢአት ይቅር ብትሉ፣ ኀጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል፤ ኀጢአታቸውን ይቅር ባትሉ ግን፣ ይቅር አይባልላቸውም።”